ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ
መግቢያ
እንደምናየውና እንደምንከታተለው የዓለም ሁኔታ እጅግ እየተወሳሰበ መጥቷል። በተለይም የጥቢው አብዮት በመባል ከሶስትና ከአራት ዐመታት በፊት በሰሜን አፍሪካ በአንዳንድ አገሮች የተካሂዱት እንቅስቃሴዎችና የለውጥ ፍላጎቶች የመጨረሻ መጨረሻ የተጠበቀውን ውጤት አላመጡም። ከዛሬ ሶስት ዐመት ጀምሮ የፕሬዚደንት አሳድን መንግስት ለመጣል የተካሄደውና የሚካሄደው እልክ አስጨራሽ ትግል ለብዙ መቶ ሺህ ሰዎች መገደል፣ መሰደድና መንገላታት፣ እንዲሁም ለጥንታዊ የታሪክ ቦታዎች መውደም ምክንያት ሆኗል። የፕሬዚደንት ሳዳም መንግስት ከተደመሰሰና ፕሬዚደንቱም ከተገደሉ በኋላ ኢራክ የሱኒቶችና የሺኢቶች መፋለሚያ በመሆን እስካሁን ድረስ ወደ ስድስት መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ሞቷል። ያን የመሰለ ጥንታዊ የታሪክ አገርና በዘይት ሀብት የተገነባ አገር አሁን ህዝቡ በድህነት የሚማቅቅበት፣ በበሽታ የሚሰቃይበትና ህይወቱ ብዠ ያለበት አገር ሆኗል። እነ ሊቢያ የመሳሰሉት ያልተሳኩ አገዛዞች(failed State) በመባል ወደ ርስ በርስ ጦርነት አምርተው ሀብት የሚወድምበትና የሰው ህይወት የሚጠፋበት አገር ሆነዋል። አምባገነኖችን ለማስወገድና የሊበራል ዲሞክራሲን ስርዓት ለማስፈን ተብሎ በምዕራቡ ዓለም ውስጥ ለውስጥ የተቀሰቀሰው ሴራና ቀጥተኛ ድጋፍ እነዚህን አገሮች እንዲበታተኑ በማድረግና ህዝቦቻቸውም ጠንካራና አለኝታ የሚሆናቸውን መንግስት ለመመስረት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አሁን ደግሞ እንዲሁ በምዕራቡ የስለላ ድርጅትና በሳውዲ አረብያና በካታር ይደገፍ የነበረው አይሲ(ISI) የሚባለው የእስላም አክራሪ ድርጅት በመስፋፋትና የካሊፋትን መንግስት ለመመስረት ባለው ፍላጎት የሱን ዕምነት የማይከተሉትን ሁሉ እያረዳቸው ነው። ወደ ዩክሬይንም ስንሄድ ራሺያን አዳክሞና በታትኖ የአሜሪካንንና የምዕራቡን ዓለም የተቀጥያ መንግስታት ለማቋቋም የተደረገው ሴራ ዩክሬንን ለሁለት እየከፈላትና ህዝብ እየተላለቀባት ነው። በአወቅኹኝ ባይነትና በማን አለኝበት በሊበራል ዲሞክራሲ፣ በነፃ ገበያና በምርጫ ስም አሳቦ በምዕራቡ ዓለም የሚካሄደው ዐይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት የእስላቭን ወንድማማች ህዝቦች ርስ በርስ እያጨራረሰው ነው።