ጸጋዬ ገብረ መድኅን አርአያ
እንደ ልጄ የምቆጥረውና ከበኩር ልጄ ከዩሐንስ ጋር ያደገው ሳምሶን በሕክምና ኮሌጅ ይማር በነበረበት ዘመን በምሽቱ ሰዓት ላይ የ‹‹ፈገግታ ጊዜ›› በምንለው ግማሽ ሰዓት ያጫውተን ነበር፡፡ አዎን ሕይወት ውጥርጥር ባለበትና ጭንቀት ከቀበሌ ከሚወረወር ቀስት፣ ጭንቀት ከየካድሬውና ከየፖለቲካው ኅቡዕ ድርጅት ከሚወረወር ሌላ ቀስት፣ ጭንቀት፣ ከመስሪያ ቤት ጭንቀት፣ ከበላይ አካል ጭንቀት፣ ከበታች አካል ጭንቀት፣ ጭንቀት ---- አንድ የድሮ ማስታወቂያ ሚኒስትር እንዳሉት ከላይ ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ በሚለቀቅብህ እሳት፣ ከታች ከሕዝቡና ከሠራተኛው ከሚነድድብህ እሳት የገና ዳቦ ትሆናለህ፡፡ ስለዚህ ‹‹በታይም አውት›› (ፋታ ልበለው) መልክ ከሳሚዬ ጋር የማደርገው የግማሽ ሰዓት ውይይት (ጨዋታ) ለእኔ “ማሳጅ” ነበር፡፡ መታሻ!
እንደ ወትሮው የዛሬው ወጋችን በክፍል ውስጥ ስለነበረው አጋጣሚ ነበር፡፡ በዚያው ዕለት በሕክምናው ኮሌጁ የመጀመሪያው ሰዓታት (ሦስት) አስተማሪው ዶክተር አሥራት ወልደየስ ነበሩ፡፡ “ዛሬ የማስተምራችሁ ስለ ጦር ሜዳ አነስተኛ የቀድዶ ሕክምና ነው” ይላሉ፡፡ አከታትለውም የጦር ሜዳውን “ሰገሌ እንበለው” ይላሉ፡፡ ይቀጥላሉ፡፡ ተፋላሚዎች በወሎው ጦር በኩል “ንጉሥ ሚካኤል” ---- ይሉና ቆም ብለው ይመለከቱ ጀመር፡፡ እንዳጋጣሚ ከፊት ለፊት የተቀመጠውን አንዱን ተማሪ “ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስን ታውቃቸዋለህ? ብለው ይጠይቁታል፡፡ “አንተዋወቅም” ይላል፡፡ ሁለተኛው ጊዜ ሳይፈጅ ወደ መርካቶ ሲኬድ መግቢያው ላይ ድልድይ ያላቸው ሰውዬ ናቸው” ይላቸዋል፡፡ ሦስተኛው በሙሉ የአዋቂነት ኩሩ ስሜት ‹‹የአጤ ኃይለሥላሴ ቅድመ አያት ናቸው፡፡ ከአያቴ ጋር በጣም ይተዋወቁ ነበር›› አለ፡፡ ሌላው የፕሮፌሰር አሥራትን ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት የበለጠ ለማጋጋል ፈለገና ይልቁንም እሳቸው በዛሬው ፕሮግራማቸው ስለጦር ሜዳ ሕክምና ለማስተማር የተዘጋጁ መሆናቸውን ስለተናገሩ “ኢትዮጵያ ከእንግሊዞች ጋር በተዋጋች ጊዜ የጦር መሪ የነበሩት አጭር፣ ፉንጋ ሰው ነበሩ፡፡ አጤ ኃይለ ሥላሴ ሠላሳ ዓመታት አሠሩአቸው” ይላል፡፡ ፕሮፌሰሩ ትንሽ ይደንቃቸውና “ኢትዮጵያ ከእንግሊዞች ጋር የተዋጋችው ትራፋልጋር ላይ ነበር ወይስ ወተርሉ ላይ ነበር?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ አራዳው ተማሪ “የለም ሰገሌና አንኮበር ላይ ነበር” ይላቸዋል፡፡ (በነገራችን ላይ እንግሊዞች በወተርሉና በትራፋልጋር ላይ ጦርነት የገጠሙት ከፈረንሳዩ መሪ ከናፖሊዮን በናፖርት ጋር ነበር፡፡) ፕሮፌሰሩ ቀልዱንም ሞክረውት ጥርሳቸው ሊላቀቅ አልቻለም፡፡ በጎጃም ቅኔ ቤት የሚወራ ጨዋታ ነበር፡፡ በጎንጅ የሚታወቁ አንድ የቅኔ መምህር ነበሩ ይባላል፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ጥርሶቻቸው ሽግናም ነበሩ፡፡ አንድ ቀን አንድ ወዳጃቸው ሰውን ሁሉ በጨዋታው ሲያስቅ ውሎአል፡፡ መምህር ሞገሴ ግን አንድም ጊዜ ፈገግ ሲሉ አልታዩም፡፡ ወደማታ ላይ ሰውየው “አባ ሞገሴ አንድ ደቂቃ እንኳ ሲስቁ አላየሁዎትም›› ይላቸዋል፡፡ ጥርሰ ሽግናሙ መምህርም ‹‹መቼ የምስቅበት ጥርስ ስጠኝና?” አሉ ይባላል፡፡ ለመሆኑስ በዚህ አገር ከማስለቀስ አልፎ የሚያስቅ ነገር ከወዴት መጥቶ! አባ ሞገሴ ጨርሰውታል፡፡ መቼ ለፈገግታ ታደልን፡፡