ህጉዳዩ ያገባናል ከምንል ሰሜን አሜሪካ ከምንኖር የቅማንት ብሄረሰብ ተዎላጆች የተላከ ደብዳቤ።
ሚያዝያ 9-2006 ዓ. ም.
ውድ ወገኖቻቸን፤ በመጀመሪያ “ታሪክን ከሥሩ፤ መጠጥን ከጥሩ” እንዲሉ፤ ለዛሬ ይህችን መልክት አዘል መጣጥፋቸን ለናንተ ለማቅረብ ሥንነሳ፤ ለተነሳንበት ቁምነገር ትርጉም ይሰጥ ዘንድ በአባቶች ምሳሌ ጀመርን። በመሆኑም፤ ትኩረታችን እና መነሻችን፤ የኢትዮጵያችን ሰሜናዊ ክ/ሀገር የሆነችው ጎንደር ላይ ሲሆን፤ መድረሻችን ደግሞ፤ በዚሁ ክ/ሀገር የሚኑሩትን እጅግ ረጅም ታሪክ ያላቸውን የቅማንት ብሔረሰብ ወገኖቻችን ወቅታዊ ችግር መሰረት ያደረግ ነው።
ጎንደር፤ በተፈጥሮ አቀማመጧ ለጠላት የማትመች፤ ለዜጎቿ ምሸግ ትሆን ዘንድ በተራሮች እና በወጣ ገባነቷ እጅግ የተዋበች የሰሜኗ ኢትዮጵያችን አንዷ አካል ነች። በዓለም ዙሪያ የማይገኙ የቀይ ቀበሮ እና ዋልያ እንሰሳት ባለቤት የሆነች። በአየር ንብረቷም፤ የወይና ደጋ፤ ደጋና ቆላማ የአየር ሁኔት የሚፈራረቁባት ክ/ሀገር ናት ። ከ300 ዓመት በላይ ያሥቆጠረ የታሪክ እና የሥልጣኔ ምንጭ ባለቤትነቷን የሚመሰክርላት የአፄ ፋሲል ግንብ የሚገኝባት፤ የውጪ ጎብኝዎች ለማዬት የሚጓጉላት ክ/ሀገራችን ጎንደር ናት።
የሕዝቧንም ሥብጥር ስንመለከት፤ እንደዛሬይቱ አዲስ አበባችን ጥንታዊ መናገሻ ስለነበረች በተለይም ከተሜው ህዝብ ከሁሉም የሃገራችን ክፍሎች በተለያዩ ምክንያቶች መጥተው ተዋህደው የሚኖሩባት፤ የኦርቶዶክስ አማኞቿን በአርባ አራቱ ታቦት ያጀበች፤ አብዛኛው ሕዝብ የኦርቶዶክስ አማኝ ቢሆንም ከዚሁ ጎን ለጎን የእሥልምና፤ የፕሮተስታንት፤ የካቶሊክ እና የመሳሰሉት ሃይማኖት አምላኪ ወገኖቻችን ያቀፈች ስትሆን፤ እንዲሁም ቋንቋ እና ባህሏንም ሥንቃኝ ደግሞ፤ አብዛኛው ህዝብ የሚናገረው የአማርኛ ቋንቋን ሲሆን፤ በሰሜን በኩል ከትግራይ ክ/ሀገር አጎራባች በመሆኗ በሁለቱ ድንበር ያለው ሕዝባችን ትግርኛ ቋንቋንም እንደ መግባቢያ ይጠቀምበታል። የዘር አመጣጡም ቢሆን፤ አማራ፤ አገው፤ ቅማንት፤ ጉምዝ፤ ወይጦ እና እንዲሁም ጨርሰው የጠፉትና የተዋጡት እነ ጋፋትም አሉበት።