የጎሳ ፌዴራሊዝም፤ የአማራው ጎሳ የጅምላ መፈናቀልና አማራውን ለማጥፋት የሚደረገው ስልታዊ የወያኔ ትግሬዎች ዘመቻ
ክፍል አንድ?
የወያኔ ትግሬዎችና ስለ አማራ ህዝብ ያላቸው ግንዛቤና የቆየ ጥላቻ ምን ይመስላል?
የወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎችም ሆኑ ተከታዮቻቸው የትጥቅ ትግላቸውን ሲጀምሩ ለትግራይ ህዝብ ችግርና ኋላ ቀርነት ተጠያቂዎቹ ከዳግማዊ ዐጼ ምንሊክ ጀምሮ እስከ ደርግ መውደቅ ድረስ በስልጣን ላይ የነበሩት ወያኔ «አማራ» ብሎ የሚጠራቸው መንግስታት እንደ ነበሩ በፖለቲካ ፕሮግራም ደረጃ ቀርጸው የትግራይን ህዝብ እንዳስተማሩ ቀድሞ የወያኔ ድርጅት አባል የነበረውና ዛሬ በስደት በሚኖርበት አውስትራሊያ ሆኖ የወያኔን እኩይ ዓላማ በቆራጥነትና በሃቅ እያጋለጠ ያለው አቶ ገብረ መድህን ዓርዓያ በቅርቡ “እነማን ነበሩ” በሚል ርእስ በመረጃ አስደግፎ አሳውቆናአል። የወያኔ ድርጅት የአማራው ህዝብ በእነዚህ «የአማራ መንግስታት» ብሎ በሚጠራቸው ከዐጼ ምንሊክ እስከ ደርግ መውደቅ ድረስ በነበሩት መንግስታት ዋነኛ ተጠቃሚ እንደነበረና የእነዚህም መንግስታት የስልጣን መሰረት እንደ ነበረ ሲያስተምር ቆይቶአል፤ ዛሬም ይህንኑ እያደረገ ነው ያለው። በዚህ ዓይነት የአማራን ህዝብ «የእነዚህ ያለፉት መንግስታት የስልጣን መሰረት ነው» በማለት ወያኔ የአማራውን ህዝብ ሲፈርጅ ቆይቶአል። የወያኔ ትግሬ መሪዎች የትግራይ ህዝብ ዐጼ ምንሊክን በመሳሰሉት «የአማራ ተወላጆች» የሆኑ የኢትዮጵያ መሪዎች እንደ ኢትዮጵያዊ እንደማይታይ ለትግራይ ህዝብ ያስተምሩ ነበር። እነዚህም «የትግራይን ህዝብ እንደ ኢትዮጵያዊ የማይቆጥሩ የአማራ መሪዎች» የትግራይን ህዝብ ሆን ብለው እንዴት ለችግር፤ ለጎስቁልናና ለእንግልት እንዳበቁት የወያኔ ድርጅት መሪዎች (ዛሬ በስልጣን ላይ ያሉትም ሆኑ ድርጅቱን ጥለው በመውጣት ዛሬ ተቃዋሚ ነን ብለው የዛሬው የትግራይ ህዝብ ሰቆቃ ከደርግ ጊዜው የባሰ ነው ብለው የሚነግሩን ጭምር) በሰፊው አስተምረዋል። እንግዲህ የወያኔ መሪዎች «የአማራ ንጉስ» ብለው በሰየሟቸው በዐጼ ምንሊክ ተጀመረ ያሉት የትግሬዎች ጭቆና ተከታዮቻቸው ናቸው በሚሏቸው የዐጼ ሃይለ ስላሴና የደርግ መንግስታትም ዘመን ቀጥሎ የትግራይ ህዝብ በመጨረሻ ተማሮ “የአማራውን የደርግ” መንግስት ለመጣል እንደ ተነሳ እንረዳለን። የወያኔ መሪዎች የትግራይን ህዝብ ችግር የአማራ ተወላጆች በሚላቸው የኢትዮጵያ መሪዎች እንደተፈጠረ አድርገው እንዴት እንደሚያዩና እንደሚቀሰቅሱ ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ እኔ በምኖርበት በሆላንድ ሀገር በስደት የሚኖረው የቀድሞው የወያኔ ድርጅት መሪና ጠቅላይ የጦር አዛዥ አረጋዊ በርሄ «ወያኔን ተቃዋሚ ነኝ» ብሎ ካለ በኋላ እንኩዋን በሚከተለው መልክ ከጻፈው ጽሁፍ እንረዳለን።